1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዉይይት፤ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ ጥቅምና ጉዳት በኢትዮጵያ

እሑድ፣ ሚያዝያ 27 2016

ኢትዮጵያ ዉስጥም የማህበራዊ መገናኛ ዘዴ መረጃን ከማሰራጨት በተጨማሪ ለብዙዎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል።የንግድና የፈጠራ ሥራ፣የሙያ፣ የምርት ማስታወቂያ፣ ለፍቅረኞች መተዋወቂያ፣ ምክር መለገሺያ፣ ማስተማሪያ፣ ለተቸገሩ ርዳታ መሰብሰቢያ፣ የኃማኖት መስበኪያ፣ ለፖለቲከኞች ሰዎችን ማደራጂያ፣ አላማና ፕሮግራምን ማስተዋወቂያ፣ የፕሮፓጋንዳ ማሰራጪያም ነዉ።

https://p.dw.com/p/4fUbj
ማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ የየማሕበረሰቡን አስተሳሰብ፣ አኗኗርና ሥነልቡና ጭምር እየለወጠዉ ነዉ
ሰፊ አገልግሎት ከሚሰጡት ከታዋቂዎቹ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መካከል ከፊሉምስል Axel Heimken/dpa/picture alliance

ዉይይት፤ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ ጥቅምና ጉዳት በኢትዮጵያ

በዛሬዉ ዉይይታችን የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ (Social Media) በኢትዮጵያ ማሕበረ-ፓላቲካዊና ምጣኔ ሐብታዊ እንቅስቃሴ ላይ ያለዉን ሚና ወይም ተፅዕኖ ባጭሩ እንቃኛለን።እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር በ1990ዎቹ ማብቂያ ግድም 6 ዲግሪ የተባለዉ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ ለዓለም ከተዋወቀ ወዲሕ  ሰዎች በግል ወይም በጋራ መረጃዎችን፣ ሐሳቦችን፣ ሁነቶችን የሚፈጥሩ፣ በፅሑፍ፣ በፎቶና ቪዲዮ የሚያደራጁ፣ ለሌሎች የሚያጋሩና የሚለዋወጡበት ሥልት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገና እየሰፋ መጥቶ ዛሬ ቢያንስ ስምንት ታዋቂ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሰፊ አገልግሎት እየሰጡ ነዉ።

እንደ ፌስ ቡክ፣ዩቱዩብ፣ ትዊተር፣ ቲክ ቶክ፣ ኢንስታግራምና ሌሎቹም የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መረጃን ፣ አጋሪዉ በሚፈልገዉ መንገድና ጊዜ ለየሚፈልጋቸዉ ወገኖች የሚያዳርሱ በመሆናቸዉ በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ፣ ተዘወታሪ እንዳዴም መደበኛ መገናኛ ዘዴዎችን ቀድመዉና ተክተዉ መረጃ እያሰራጩ ነዉ።

ኢትዮጵያ ዉስጥም የማህበራዊ መገናኛ ዘዴ መረጃን ከማሰራጨት በተጨማሪ ለብዙዎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል።የንግድና የፈጠራ ሥራ፣የሙያ፣ የምርት ማስታወቂያ፣ ለፍቅረኞች መተዋወቂያ፣  ምክር መለገሺያ፣ ማስተማሪያ፣ ለተቸገሩ ርዳታ መሰብሰቢያ፣ የኃማኖት መስበኪያ፣ ለፖለቲከኞች ሰዎችን ማደራጂያ፣ አላማና ፕሮግራምን ማስተዋወቂያ፣ የፕሮፓጋንዳ ማሰራጪያም ነዉ።

የዚያኑ ያክል ግለሰቦች ወይም ቡድናት የሚፈልጉትን ግለሰብ፣ ቡድን፣ ፓርቲ፣ ጎሳ መንግስት ወዘተ ሐሳብ፣ አላማና እርምጃን ለሌሎች ለማስተዋወቅ፣ ለማስፋፋትና ለማስረፅ፣ የማይፈልጉትን ወይም ተቃራኒያቸዉን ለማሳጣት፣ለመስደብ፣ለማንቋሸሽ በሐሰት መረጃ ለመወንጀልም ይጠቀሙበታል።

ማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ለማሕበረሰቡ ከፍተኛ አገልግሎት የመስጠታቸዉን ያክል የአደጋና የሥጋትም ምንጭ ናቸዉ
በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚሰራጩ ዘገቦች፣ ምሥልና መልዕክቶችን ትክክለኛነት ማጣራት ይቻላል?

ዘገቦች እንደሚጠቁሙት የኢትዮጵያ መንግስት፣ አንዳድ የክልል መስተዳድሮች፣ የተለያዩ ተቋማትም ጭምር የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ «ሠራዊት» ወይም አንቂ የሚል ስብስብ አደራጅተዉ የመንግስትን፣ የየመስተዳድር፣ የየተቋማቱንና  ባለሥልጣናቱን ገፅታ ለማጎልበት፣ የሐሳብ፣ አቋም እርምጃቸዉን ትክክለኛነት ለማስረፅ፣ ተቀናቃኞቻቸዉን ለማንኳሰስ ማሕበራዊ መገናኛ ዘዴን በዘመቻ መልክ ይጠቀሙባታል።

የተወሰኑትም ቢሆኑ የዚሕ መሰሉ ስብስብ አባላት ባደባባይ ሲሸለሙም ቢያንስ በቴሌቪዥን ዓይተናል።ልምዱን ተቃዋሚ ፖለቲከኞች፣ ማሕበራት፣ ቡድናት፣ የኃይማኖት ስብስቦችም ጭምር እየተከተሉት ነዉ ይባላል።

የዚያኑ ያክል በየጊዜዉ፣ በየምክንያቱና በየአካባቢዉ የኢንተርኔት አገልጎሎት መቋረጡ ለበጎም ይሁን ለመጥፎ ያለሙ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ ሥራዎችን እያወከ መሆኑን የመብት ተሟጋቾች በተደጋጋሚ ይዘግባሉ።የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ አገልግሎት በኢትዮጵያ ያለበት ደረጃ፣ ጥቅምና ጉዳቱ የዛሬ ዉይይታችን ትኩረት ነዉ።

ነጋሽ መሐመድ