1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ጤናየመካከለኛው ምሥራቅ

ከባድ አካል ጉዳተኛ ልጅን የምትንከባከበዋ ወጣት

ልደት አበበ
ዓርብ፣ ግንቦት 9 2016

ትዕግሥት ዱባይ ውስጥ አንድ ከባድ የአካል ጉዳተኛ ልጅን የምትንከባከብ ኢትዮጵያዊት ወጣት ናት። ሀገር ውስጥ አማራጭ ማጣቷ ወደ ስደት እንደዳረጋት የምትናገረው ይቺው ወጣት ሥለ ሥራዋ ፈተና እና ሌሎችን ለመርዳት ያላት ፍቅር ገልፃልናለች።

https://p.dw.com/p/4fvoq
Pflege
ምስል Sebastian Gollnow/dpa/picture alliance

ከባድ አካል ጉዳተኛ ልጅን የምትንከባከበዋ ወጣት

ብዙውን ጊዜ ወደ አረብ ሀገራት ለሥራ የሚሄዱ ሴት ኢትዮጵያውያን በቤት ፅዳት ወይም ምግብ አብሳይነት ስራ ተቀጥረው እንደሚሰሩ ይናገራሉ። ወጣት ትዕግሥት ግን ከዚህ ከበድ ላለ ስራ ወስናለች። ትዕግሥት 27 አመቷ ነው። የክፍለ ሀገር ልጅ ናት። ከስድስት ዓመት በፊት ለስራ ወደ ዱባይ ስትሄድ በቤት ሰራተኝነት ነበር። ኃላም ስራዋን ለመቀየር ተገደደች። እሷም አዲሱን ስራ የተቀበለችው እዛው ዱባይ እንድትቆይ እና ገንዘብ ለማግኘት ስትል ነው።  « የሚያመው ልጅ ነው የምንከባከበው። በራሱ በሰው እገዛ ነው። በራሱ የሚያደርገው ምንም ነገር የለም» የምትለው ወጣት 24 ሰዓት ውሎዋ ከታማሚው የ29 ዓመት ወጣት ጋር እንደሆነ ገልፃልናለች። ይህ የስነ ልቦና ጉዳት መፍጠሩ አይቀሬ ነው። « እሱ በተኛ ሰዓት መተኛት ሲነቃ መንቃት አለብኝ ትላለች» ይህንንም ስራ የምትሰራው ኢትዮጵያ ያለው ቤተሰቦቻን ለመርዳት ያላት አማራጭ ይህ ብቻ ስለሆነ ነው። 

ሊባኖስ ውስጥ በቤት ሰራተኝነት ተቀስራ የምትሰራ ኢትዮጵያዊት ልብስ ስታሰጣ
ሊባኖስ ውስጥ በቤት ሰራተኝነት ተቀስራ የምትሰራ ኢትዮጵያዊት ልብስ ስታሰጣምስል picture-alliance/AP Photo/G. Kassab

የስራው ክብደት

የትዕግሥትን ሥራ ከባድ የሚያደርገው ሌላው ነገር የምትንከባከበው ልጅ መናገርም ሆነ መስማት አለመቻሉ ነው። ስለ በሽታው ምንነትም ይሁን ከታመመ ስንት ጊዜ እንደሆነው አታውቅም። « አይናገርም። አይንቀሳቀስም። ምንም ነገር አይልም። አይተናኮልም። ግን ድምፁ ይረብሻል። ይጮኻል።»ትዕግሥትን እንደ ስሟ ትዕግስተኛ ያደረጋት ነገር ምን ይሆን? እሷ እንደምትለው ኢትዮጵያ ትምህርት ቤት እያለች በበጎ ፍቃደኝነት ቀይ መስቀል ውስጥ በፈረቃ ታግዝ የነበረው ስራ ብዙ አስተምሯታል። « ታማሚዎች ሲደውሉ አካባቢያቸውን በመጠየቅ ርዳታ እንሰጣለን። ቀይ መስቀሉ እኛን የመጀመርያ ርዳታ እንዴት መስጠት እንዳለብን ያሰለጥነናል። » ይህም ስልጣና አሁን የምትሰራው ስራ እንዳይከብዳት ረድቷታል። ለእሷ ፈተና የሆነባት ነገር የፆታ ልዩነታቸው ነበር። 

ከሳውዲ የተመለሰች ኢትዮጵያዊት መታወቂያዋን ለ IOM ሰራተኞች ስታሳይ
ምስል Michele Spatari/AFP

ሥራውን እንዴት አገኘች?

ሥራው ከባድ ሆኖም ትዕግሥት ሌሎችን መርዳት መቻሏ ያስደስታታል። ቀጣሪዎቿንም ማሳመን ችላለች። « እዚህ ቤት ፅዳት ስሰራ ልጁ በጣም ያሳዝነኝ ስለነበር በመኃል እየሄድኩ አየዋለሁ። የምትይዘውን ልጅ አግዛለሁ። እና ያን ያን በማየት ነው ወደዚህ ስራ ያሸጋሸጉኝ። » ትላለች። ወደ ዱባይ ከሄደች አምስት ዓመት የሆናት ትዕግሥት በመሀል ወደ ኢትዮጵያ ተመልሳ ነበር። ይሁንና ነገሮች ስላልተስተካከሉላት ለመመለስ ግድ ብሏታል። « ከደሀ ቤተሰብ ነኝ። እህትም ወንድምም አሉኝ። የተሻለ ህይወት አይደለም የምንኖረው እና ለዛ ነው።» ቤተሰቦቿም ስለምትሰራው ስራ ያውቃሉ። 

ትዕግሥትን የህይወት ተሞክሮዋ ያስተማራት ነገር 

« ዐረብ አገር ሲባል ቀለል ያለ ስራ እንጂ እንዲህ አይነት ስራ የምንሰራ አይመስለንም። ከሀገር ስንወጣ ማንኛውንም ከባባድ ነገሮች ለመቀበል ዝግጁ መሆን አለብን። ካለበለዚያ በጣም ነው የሚጨንቀው ፤ የሚከብደውም። » የምትለው ትዕግሥት አሁን የምትሰራውን ስራ «ባይመቻትም» አዕምሮዋ መቀበል ግድ ይለዋል።  ይህንን ስራ ለምን ያህል ጊዜ መስራት እንደምትችል አታውቅም። ለጊዜው ቀጣሪዎቿ እስካረዘሙላት ድረስ እዛው ለመቆየት ወስናለች።  « የተሻለ ነገር ባገኝ አይዙኝም። » ስትል ቀጣሪዎቿ በፈለገችው ጊዜ እንደሚያሰናብቷት ፍቃደኛ መሆናቸውን ትገልፃለች። 

ትዕግሥት ኢትዮጵያ እስከ 10ኛ ክፍል ድረስ ተምራለች። «ውጤት ሳይመጣልኝ ሲቀር ነው የተሰደድኩት» የምትለው ወጣት ምናልባት የበለጠ «ትምህርቴ ላይ አተኩሬ ቢሆን ኖሮ» ብላ የሚፀፅታት ነገር ይኖር ይሆን? ወይስ  የተቻላትን ሁሉ አድርጋለች? እሷ ሁሉን አድርጌያለሁ ትላለች።  እድሉን ብታገኝ በትምህርት የተደገፈ ርዳታ አግኝታ ወደፊት በዚህ የሙያ ዘርፍ ማገልገል ብትችል ምኞቷ ነው።

ልደት አበበ

ታምራት ዲንሳ