1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአሜሪካዉ አምባሳደር መግለጫ ላይ የባለሙያዎች አስተያየት

ዓርብ፣ ግንቦት 9 2016

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሀገሪቱ የተመረጠን መንግሥት በኃይል ለመገልበጥ የተነሱ ያላቸውንና ሰላማዊ ዜጎችን በማፈንና በማሸበር የሚታወቁ ሲል የገለፃቸውን ኃይሎችን የጠቀሰ መሆኑን በመግለጽ የአምባሳደሩን መግለጫ ውድቅ አደረገ። አምባሳደር ተፈራ ሻውል እንደሚሉት ሀገራት ወዳጅ የሚሉትን ሀገር ይመክሩ እንጂ ጠምዝዞ ማሰራት ከመርህ አንፃር አይቻልም።

https://p.dw.com/p/4g08t
የኢትዮጵያ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር
የኢትዮጵያ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ምስል Solomon Muchie/DW

በአሜሪካዉ አምባሳደር መግለጫ ላይ የባለሙያዎች አስተያየት

የአሜሪካ አምባሳደር ስለ ኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የሰጡት መግለጫ የባለሙያ አስተያየት

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ የኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ውንጀላ አቅርበዋል ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። መንግሥት ሀገሪቱን እንዴት መምራት እንዳለበትም ያልተጠየቁትን ምክር ለግሰዋል ያለው ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አምባሳደሩ ትርጉም የማይሰጡ እና ያልተጤኑ ያላቸውን ሀሳቦችን በንግግራቸው ማንፀባረቃቸውን በመጥቀስ አጣጥሎታል። አንድ አንጋፋ ዲፕሎማት አምባሳደሩ ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ይሁንታ ሳያገኙ ይህንን አይናገሩም ብለዋል። "አንዳንድ ጊዜ ግን ነገሮች ከመስመር ለቀቅ ሲያደርጉ ሀቁን መናገር የወዳጅነት ምልክት ነው" በማለት የአምባሳደሩ ንግግር ለወዳጅ ሀቁን ከመናገር የመነጨ ሊሆን እንደሚችልም አመልክተዋል። አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ኢትዮጵያ ውስጥ በግጭት ላይ ያሉ ወገኖች ጊዜያዊ ሀገር አቀፍ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጠይቀዋል።

በኢትዮጵያ የአሜሪካው አምባሳደር ምን አሉ? 

ብዙ ጊዜ ከመገናኛ ብዙኃን የማይጠፉት በኢትዮጵያ የዩናይትድ ስቴስት አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ከትናንት በስቲያ አዲስ አበባ ውስጥ ባደረጉት ንግግር በተዋጊዎች መካከል ጊዜያዊ ሀገር አቀፍ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጠይቀዋል። አምባሳደሩ የሰጡትን የፖሊሲ መግለጫ የተሳሳተ እንዲሁም የመረጃ ጉድለት ያለበት ነው ያለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ መግለጫው "የኢትዮጵያን እና የአሜሪካን ታሪካዊ እና ወዳጃዊ ግንኙነት የሚፃረር ነው" ብሎታል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያን በተመለከተ የአሜሪካው አምባሳደር እየሰጡት ያለው መግለጫ ከዲፕሎማሲያዊ የግንኙነት መርህ እንፃር ምን ማለት ነው? ሲል ዶቼ ቬለ የጠየቃቸው አንጋፋው ዲፕሎማት አምባሳደር ተፈራ ሻውል ተከታዩን ብለዋል።

"አሜሪካኖች አይተውታል። ሁሉን ነገር። ከመንግሥትም ወገን ሆነው፣ ከአማጺያንም ወገን ሆነው አይተውታል። አሁን ሁሉም መሳሪያ ተኩስ አቁሙ ነው ያሉት። እና ይህ አሜሪካኖቹ ጋርትንሽ የእይታ ለውጥ ታያለህ" 

ኤርቪን ማሲንጋ፤ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር
ኤርቪን ማሲንጋ፤ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ምስል Seyoum Getu/DW

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምላሽ 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሀገሪቱ የተመረጠን መንግሥት በኃይል ለመገልበጥ የተነሱ ያላቸውን እና ሰላማዊ ዜጎችን በማፈን እና በማሸበር የሚታወቁ ሲል የገለፃቸውን ኃይሎችን የጠቀሰ መሆኑን በመግለጽ የአምባሳደሩን መግለጫ ውድቅ አድርጓል። አምባሳደር ተፈራ ሻውል እንደሚሉት ሀገራት ወዳጅ የሚሉትን ሀገር ይመክሩ እንደሆን እንጂ ጠምዝዞ ማሰራት ግን ከመርህ አንፃር አይቻልም። 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከወጣው መግለጫ ባለፈ ዝርዝር ከመናገር ተቆጥቧል። ራስን መከላከል የሁሉም ሀገራት መብት መሆኑን የገለፁት የአሜሩካው አምባሳደር ታጣቂዎች ከንግግር ይልቅ በሁከት ፖለቲካዊ ዓላማዎችን ለማሳካት ከሞከሩ ለበደሎች መፈፀም በር ከፋች ነው ብለዋል። አምባሳደር ተፈራ ሻውል "አንዳንድ ጊዜ ነገሮች ከመስመር ለቀቅ ሲያደርጉ ሀቁን መናገር የወዳጅነት ምልክት ነው" ሲሉ የንግግሩን ጭብጥ አመልክተዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአሜሪካን ጨምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ ተቀማጭ የሆኑ ኤምባሲዎች የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሁኔታ በተመለከተ በጋራ መግለጫዎችን እያወጡ ሲሆን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም እግር በእግር እየተከታተለ የመልስ መግለጫ በማውጣት ላይ ይገኛል።

ሰለሞን ሙጬ 

አዜብ ታደሰ 

ታምራት ዲንሳ