1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአማራ ክልል የጥምቀት በዓል እንዴት አለፈ?

ሰኞ፣ ጥር 13 2016

የጥምቀት በዓል አከባበር በአማራ ክልል ካለው የፀጥታ ሁኔታ አንፃር ችግር ሊፈጠር ይችላል የሚል ሰፊ ስጋት አሳድሮ ነበር፡፡ የክልሉ መንግሥት እንዳለው ግን በዓላቱ ያለምንም የፀጥታ ችግር ተከብረው ተጠናቅቀዋል፡፡ያም ሆኖ በአንዳንድ የምስራቅና ምዕራብ ጎጃም አካባቢዎች በዓሉ በቤተክርስቲያናት አጥር ግቢ ብቻ መከበሩንነዋሪዎቹ አመልክተዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4bYN0
የዘንድሮው ጥምቀት በጎንደር
የዘንድሮው ጥምቀት በጎንደር ምስል Michele Spatari/AFP/Getty Images

በአማራ ክልል የጥምቀት በዓል እንዴት አለፈ ?


በአማራ ክልል ካለው የፀጥታ ሁኔታ አንፃር በየአመቱ ጥር 11 የሚከበረው የጥምቀት በዓል አከባበር ላይ ችግር ሊፈጠር ይችላል የሚል ሰፊ ስጋት አሳድሮ ነበር። የአማራ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ደ/ር መንገሻ ፋንታው ዛሬ በተለይ ለዶይቼ ቬሌ እንደተናገሩት ግን በዓላቱ ያለምንም የፀጥታ ችግር ተከብረው ተጠናቅቀዋል።

በተለይ ጥምቀት በድምቀት ከሚከበርባቸው ከተሞች መካከል አንዷ በሆነችው በጎንደር ከተማ በቅርቡ የነበረው የፀጥታ ሁኔታ  የበዓሉ አከባበር  ጥላ ያጠላበታል ቢባልም በዓሉ በልዩ ድምቀት ተከብሯል ነው ያሉት ዶ/ር መንገሻ፡፡

የጥምቀት አከባበር በባህር ዳር
የጥምቀት አከባበር በባህር ዳር ምስል Alemnew Mekonnen/DW

የከተራና የጥምቀት በዓላት ያለምንም የፀጥታ ችግር በጎንደር መከበሩን ደግሞ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ሀገረ ስብከት ፀሐፊ በኩረስየማን የዓይእሸት ሞገስ ለዶይቼ ቬሌ በስልክ አረጋግጠዋል፡፡

ጥምቀት በጃን ሜዳ ሲከበር “በረሐብ ተቆራምደው ዕለተ ሞታቸውን” ለሚጠብቁ ዕገዛ እንዲደረግ አቡነ ማትያስ ጥሪ አቀረቡ

በምሥራቅ ጎጃም ዞን አማኑኤል ከተማም የከተራና የጥምቀት በዓላት ያለምንም ችግር መከበራቸውን አንድ የከተማው ነዋሪ ተናግረዋል፡፡በምዕራብ ጎጃም ዞን የፈረስ ቤት ከተማ አስተያየት ሰጪም መንም እንኳ በዓሉ የቀድሞ ድምቀቱ ባይኖርም በሰላም መከበሩን አመልክተዋል፡፡

በደቡብ ወሎ ዞን የደሴ ከተማ አስተዳደር ነዋሪም በተመሳሳይ የዘንድሮው የከተራ፣ የጥምቀትና የቃና ዘገሊላ በዓላት በሰላም መከበራቸውን ገልጠዋል።

የጥምቀት አከባበር በባህር ዳር
የጥምቀት አከባበር በባህር ዳር ምስል Alemnew Mekonnen/DW

በባህር ዳር ከተማም ብዙ ቁጥር ያለው ህዝብ የከተራን፣ የጥምቀትንና የቃና ዘገሊላን በዓላት ወጥቶ ማክበሩን ዶይቼ ቬሌ ተመልክቷል፡በአንዳንድ የምሥራቅና ምዕራብ ጎጃም አካባቢዎች ካለው የፀጥታ ሁኔታ አንፃር ታቦታቱ ወደ ጥምቀተ ባህር ሳይወርዱ በቤተክርስቲያናት ቅጥር ግቢ ብቻ መከበራቸውን ነዋሪዎቹ አመልክተዋል፡፡

ታቦታቱ ወደ ጥምቀተ ባህሩ እንዳልወረዱ አስተያየታቸውን ከሰጡን ነዋሪዎች መካከል በምሥራቅ ጎጃም ዞን የቢቸና፣ በምዕራብ ጎጃም ዞን ደግሞ የደንበጫ፣ የአዴትና የቡሬ ከተማ አስተያየት ሰጪዎች ይጠቀሳሉ።

የጥምቀት በአል ዝግጅትና የፀጥታ ቁጥጥር በአዲስ አበባ

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ በጽሁፍ በሰጡት መግለጫ “የከተራ፣ የጥምቀትና የቃና ዘገሊላ በዓላት በሁሉም አካባቢዎች ሀይማኖታዊ ስርዓታቸውን ጠብቀው በሰላማዊና በደማቅ ሁኔታ ተከብረው ተጠናቅቀዋል” ብለዋል፡፡

ዓለምነው መኮንን
ኂሩት መለሰ